A 12 years old Kid Driving isuzu in Ethiopia




Ethiopia Dilla
በዲላ ከተማ አንድ የ12 ዓመት ታዳጊ አይሱዙ የጭነት መኪና በከተማዋ መሀል ሲያሽከረክር መያዙን የከተማዋ ፖሊስ ጽህፈት ቤት አስታወቀ ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የመንገድ ትራፊክ አደጋ መከላከል ክፍል ሃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር አሰፋ ዓለሙ በዲላ ከተማ በርካታ የትራፊክ ፍሰት በሚታይበት ቦታ ላይ አንድ የ12 ዓመት ታዳጊ አይሱዙ የጭነት መኪና ሲያሽከረክር ተይዟል፡፡

በዲላ ፖሊስ ጣቢያ እንዲቆይ የተደረገው ታዳጊ ቤተሰቡ ተጠርተው ሲጠየቁ ታዳጊው በመኖሪያ ቤቱ ግቢ ቆሞ የነበረውን አይሱዙ የጭነት መኪና ሹፌሩ ለምሳ እንደወጣ ከቤት ቁልፍ በመስረቅ ሊያሽከረክር መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ታዳጊው እድሜው ለማሽከርከር የማያበቃውና የመንጃ ፈቃድ የሌለው ሲሆን ፥ ባለማወቅ ከቅጣት ማምለጥ ስለማይቻል ቤተሰቡ አምስት ሺህ ብር ለከተማዋ መንገድ ትራንስፖርት እንዲከፍሉ በማድረግ መንጃ ፈቃድ ያለው የመኪናው አሽከርካሪ መኪናውን እንዲወስድ መደረጉንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የዲላ ከተማ መንገድ ትራንስፖርት ዩኒት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጋንዶ ስለሁኔታዉ ተጠይቀው ህብረተሰቡ ከፍተኛ አደጋ ሊያሰከትሉ የሚችሉ ተሽከርካሪዎችን ቁልፍ በአግባቡና በጥንቃቄ ሊያስቀምጥ እንደሚገባና ታዳጊው በከተማው መሃል አስፋልት ለደቂቃዎች ሲያሽከረክር በአጋጣሚ አደጋ ሳያስከትል በከተማው ትራፊክ ፖሊሶች ሊያዝ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

በዲላ ከተማ በርካታ ታዳጊ ህጻናት ከትራፊክ ፖሊስ አባላት በመሸሸግ በውስጥ ለውስጥ መንገዶች ላይ ባለሁለት እግር ሞተር ሳይክሎችን እያሽከረከሩ አደጋ በማደረስ ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት አቶ ደሳለኝ ፖሊስ ብቻውን የሚያደርገው እንቅስቃሴ ውጤት የማያመጣ መሆኑን በመረዳት ህብረተሰቡን ድርጊቱን የሚፈጽሙትን በማጋለጥ ከእንደዚህ አይነት አደጋዎች እራሱን ሊጠብቅ እንደሚገባ ተናግረዋል።
source fanabc

0 comments :