Newly Appointed American ambassadors


በኢትዮጵያ አዲሷ የአሜሪካ አምባሳደር ፓትሪሺያ ሃስላክ መስከረም 15 ቀን 2006 ዓ.ም. በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በተካሄደ ሥነ ሥርዓት የሹመት ደብዳቤያቸውን ለፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ካቀረቡ በኋላ በይፋ ሥራቸውን ጀመሩ፡፡

አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ አምባሳደር ሃስላክን ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስተዋውቅ ቪዲዮ ያዘጋጀ መሆኑን አስታውቆ፣ ይህንኑ ቪዲዮ በዩቲዩብ ላይ ማግኘት እንደሚቻል አስረድቷል፡፡

‹‹በከፍተኛ ጥራት የተዘጋጀው የዚህ ቪዲዮ ቅጂ በኤምባሲው ፕሬስ ቢሮ የሚገኝ በመሆኑ፣ ማንኛውም ፍላጎት ያለው አካል ቪዲዮውን ወስዶ ማሠራጨት ይችላል፤›› በማለት ኤምባሲው አስታውቋል፡፡

አምባሳደት ፓትሪሺያ ኤም ሃስላክ የሕይወት ታሪካቸው እንደሚያስረዳው፣ እ.ኤ.አ. ኦገስት 14 ቀን 2013 በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር በመሆን ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡ አምባሳደር ሃስላክ ከዚህ ቀደም የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አዲስ ባቋቋመው የግጭትና መረጋጋት ኦፕሬሽኖች ቢሮ ምክትል ዋና ረዳት ሚኒስትር ሆነው ማገልገላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚያ በፊት ደግሞ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የሥራ አመራር ምክትል ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የኢራቅ ሽግግር አስተባባሪ ነበሩ ተብሏል፡፡ በዚህ ኃላፊነታቸውም በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ በኩል አሜሪካ በኢራቅ ያደረገችውን ከወታደራዊ ወደ ሲቪል ኦፕሬሽኖች የመሸጋገር ሒደት ከዋሽንግተን ማስተባበራቸውን ኤምባሲው አስታውቋል፡፡ ይኸው ሒደትም እ.ኤ.አ. በዲሴምበር 2011 መጨረሻ የአሜሪካ ወታደሮች ከኢራቅ ሲወጡ መጠናቀቁን አስረድቷል፡፡

አምባሳደር ሃስላክ በሽግግር ላይ ባሉ አገሮች የሚካሄዱ የልማት ሥራዎችን በማስተባበር ረገድ ያካበቱትን ረዥም የሥራ ልምድ ይዘው ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው የተነገረ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. ከጁን 2010 እስከ ማርች 2011 የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የረሃብ ማስወገድና ምግብ ዋስትና መርሐ ግብር (ፊድ ዘ ፊውቸር) የዲፕሎማሲ ሥራ ምክትል አስተባባሪ ሆነው ማገልገላቸው ተገልጿል፡፡ ከጁላይ 2009 እስከ ጁን 2010 ደግሞ በኢራቅ የአሜሪካ ኤምባሲ የሽግግር ወቅት ዕርዳታ ጉዳዮች ረዳት አምባሳደር በመሆን የልማትና የዕርዳታ መርሐ ግብሮችን የማሸጋገር ሥራን በበላይነት ማስፈጸማቸው በኤምባሲው መግለጫ ተካቷል፡፡ የአፍጋኒስታን ጉዳይ ቢሮ ዳይሬክተር በነበሩበት እ.ኤ.አ. ከ2002 እስከ 2004 አምባሳደር ሃስላክ፣ ብዙ ቢሊዮን ዶላር የወጣበትን የመልሶ ግንባታ መርሐ ግብር መምራታቸው ተነግሮላቸዋል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2007 እስከ 2009 በእስያ ፓስፊክ የኢኮኖሚ ትብብር መድረክ (አፔክ) የአሜሪካ አምባሳደር ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2004 እስከ 2007 በላኦስ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የአሜሪካ አምባሳደር እንደነበሩ፣ በተጨማሪም በፓኪስታን የኢኮኖሚ ቆንሲል፣ በኢንዶኔዢያና በናይጄሪያ ደግሞ ምክትል የኢኮኖሚ ቆንሲል ሆነው አገልግለዋል ተብሏል፡፡ አምባሳደር ሃስላክ የሥራ ሕይወታቸውን የጀመሩት በፌዴራሉ መንግሥት ውስጥ በግብርና ሚኒስቴር እንደሆነ፣ እ.ኤ.አ. ከ1987 እስከ 1990 የአካባቢው አገሮች የግብርና አታሼ በመሆን በህንድ ተመድበው መሥራታቸው ተመልክቷል፡፡ ከዚህ ምደባ በኋላ ወደ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በመሸጋገር በአውሮፓ ኅብረት የአሜሪካ ልዑክ አባል በመሆን 24 አገሮች በአባልነት ለተካተቱበት ቡድን የሚደረግ ድጋፍ መሪ እንደነበሩ ተጠቁሟል፡፡

የአሜሪካ ኤምባሲ መግለጫ እንደሚያመለክተው፣ አምባሳደር ሃስላክ ባከናወኗቸው ስኬታማ ተግባራት የተነሳ በርካታ ሽልማቶችን ለመሸለም በቅተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2004 በአፍጋኒስታን ላከናወኑት የመልሶ ግንባታ ሥራ የተበረከተላቸው የላቀ የክብር ሽልማት፣ እ.ኤ.አ. በ2002 በበጎ ተፅዕኖና በአዘጋገብ ወጥነት ያገኙት የዳይሬክተር ጄኔራል ሽልማት፣ በተመሳሳይ ዓመት በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ አፈጻጸም ላበረከቱት እጅግ የላቀ አስተዋጽኦ ያገኙት የኸርበርት ሳልዝማን ሽልማት፣ እንዲሁም እ.ኤ.አ. በ1998 በጠንካራ የቋንቋ አጠቃቀምና ተያይዞ ባለው ባህል ላይ ላደረጉት ጥናት የተሸለሙት የሲንክሌር ላንጉዌጅ ሽልማት ጥቂቶቹ መሆናቸውን ኤምባሲው አስታውቋል፡፡

በኦሬገን፣ የሌክ ኦስዌጎ ተወላጅ የሆኑት አምባሳደር ሃስላክ ስፖኬን፣ ዋሺንግተን ከሚገኘው ጎንዛጋ ዩኒቨርሲቲ በባችለር ኦፍ አርት ዲግሪ የተመረቁ ሲሆን፣ ከኒውዮርኩ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች የማስተርስ ዲግሪ፣ እንዲሁም ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ የምዕራብ አውሮፓ ኢንስቲትዩት ሰርተፊኬት ማግኘታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ አምባሳደር ሃስላክ ሺሪንና ኪራን ኸርበርት የሚባሉ የሁለት ሴት ልጆች እናት ናቸው፡፡

0 comments :